admin
Mon, 01/20/2025 - 12:44
ሀይረንዚ ትምህርት ቤት ካስፈተናቸው 98 ተማሪዎች 76ቱ የህክምና ሳይንስ የማጥናት እድል አገኙ፡፡
====================================
ለተሻለ የትምህርት ጥራት መረጋገጥ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ስራጅ ፈጌሳ ገለፁ፡፡
በስልጤ ልማት ማህበር የተቋቋመው የሀይረንዚ ልዩ 2ተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት የ2010 የብሔራዊ ፈተና የማትጊያና የሽልማት ፕሮግራም አካሂዷል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ስራጅ ፈጌሳ የስልጤ ልማት ማህበር ሲቋቋም በዞኑ የነበረው የመሰረተ ልማት ችግር ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ሰዓት ይህ ሁኔታ መቀየሩን ተናግረው ለዚህም ጠንካራና ለልማት ወደ ኃላ የማያውቅ ህ/ሰብ መኖሩና ይህም በጠንካራ አመራር መታገዙ መሆኑን ገለፀዋል፡፡
የት/ት ቤቱ መቋቋም ለዞኑና ለክልሉ ብቻ ሳይሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሳይንቲስቶችን ለማፍራት ያለመ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ስራጅ የተገኘው ውጤትም የተያዘውን ዓላማ ስኬት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው በዞኑ የትምህርት ልማት በተለይ ከተሳትፎ አንፃር ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱንና በትምህርት ጥራት በኩል ግን ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ አንስተው የሀይረንዚ ትምህርት ቤት መቋቋም ለዚህ አጋዥነነቱ የጎላ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ብ/ብ/ህ/ክ/መ/ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር እሸቱ ከበደ እንደሀይረንዚ ያሉ ት/ት ቤቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት ከፍተኛ እገዛ እንዳላቸው ገልፀው በሀገር አቀፍ ደረጃ 6 መቶና ከዚያ በላይ ካመጡ ተማሪዎች መካከል 27 ተማሪዎችን በመያዝ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ደቡብ ክልል 2ተኛ መውጣቱን ገለፀው ለዚህም ሀይረንዚ የአንበሳውን ድርሻ መያዙን ተናግረዋል፡፡
ት/ት ቤቱ በ2008 ለመጀመሪያ ጊዜ ካስፈተናቸው 98 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች 75 አራት ነጥብ ሲያመጡ 42 ሁሉንም የት/ት አይነት ኤ /A/ አስመዝግበዋል፡፡ በ2ተኛ ዙርም ውጤቱ ተሻሽሎ ከ97 ተማሪዎች ውስጥ 94ቱ 4ነጥብ 88ቱ በሁሉም የት/ት አይነት ኤ/A/ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በ2010የተ/ት ዘመን 12ተኛ ብሄራዊ ፈተና ካስፈተናቸው 98 ተማሪዎች ውስጥ 96ቱ ከ5 መቶ በላይ ሲያስመዘግቡ 8ቱ 6 መቶና ከዚያ በላይ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡
በማትጊያ ስነ-ስርዓቱ ተማሪዎች ፥መምህራንና ሌሎች ለውጤቱ አስተዋጽኦ የነበራቸው አካላት ተሸላሚ ሲሆኑ ተማሪዎች ላብቶፕ ኮምፒውተርና የመማሪያ ቁሳቁስ፥ የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በመጨረሻም የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ህብረተሰቡ ብዙም ሳይተርፈው ከኑሮው ቀንሶ የትምህርት ስራውን እንደሚደግፍ አስታውሰው ተማሪዎቹ በቀጣይ ጉዟቸው የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ ለማሳካት ጠንክረው መማር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
Image
