Skip to main content
የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላበት የልማት ስራ ውጤታማ እንደሚሆን የሀይረንዚ ልዩ 2ኛ ደረጃ ና መሰናዶ ት/ቤት አንዱ ማሳያ ነው አሉ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ ።
በ2011 ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተና ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የሀይረንዚ ልዩ 2ኛ ደረጃ ና መሰናዶ ት/ቤት የ10ኛ ና 12 ኛ ክፍል ተማሪዎች የማትጊያ ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
በደቡብ ክልል በብሄረሰብ ልማት ማህበር ጥላ ስር ከተቋቋሙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መካከል በስልጤ ልማት ማህበር ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በ2006,የመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፉንም አጠናቆ በ2007 ዓ/ም የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረውና ውጤታማ የሆነው የሀይረንዚ ልዩ 2ኛ ደረጃ ና መሰናዶ ት/ቤት አንዱ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው ዓመት በተመዘገበው ከፍተኛ የብሄራዊ ፈተና ውጤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀዳሚነቱን ሲይዝ የሀይረንዚ አዳሪ ት/ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃውን መቀዳጀቱ የሚታወስ ሲሆን ት/ቤቱ በ2011 ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተና ላይ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎቹ ዛሬም የማትጊያ ስነ ስርዓት የፌዴራል፣የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ባለሃብቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣የተማሪ ወላጆች፣ የዞንና ወረዳ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት እውቅና ሰጥቷል።
ይህ ብቻ አይደለም ከሀይረንዚ በተጨማሪ በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች በ2011 ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተና ላይ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በማትጊያው እንዲካተቱ ተደርጓል።
በማትጊያ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ መንግስት መላውን ማህበረሰብ ና አጋር አካላትን በማስተባበርና ራሳቸው አካባቢያቸውን እንዲያለሙ በሰጠው ዕድል በዞኑ በከፍተኛ ሁኔታ የትምህርት ተደራሽነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ይሁንና በተሳትፎው ልክ ጥራትን ማሻሻል አለመቻሉን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ በንግግራቸው አስቀምጠዋል።
የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላበት የልማት ስራ ውጤታማ ነው ያሉት አቶ ዘይኔ ት/ቤቶች የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ህብረተሰቡ በ2011 ዓም 40•5 ብር ሚሊየን የሚገመት ድጋፍ በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበትና ማቴሪያል ድጋፍ ማድረጋቸውን በመግለፅ
በተጨማሪ የከተማ ባለሃብቱና የንግዱ ማ/ሰብ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ጥራቱን በሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው ብለዋል።
ማህበረሰቡ በትምህርት መስፋፋትም ሆነ በጥራት ማሻሻል የሚያደርገው ጥረት የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ነው ሲሉም ዋና አስተዳዳሪው አሞካሽተዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳና የኢፌድሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ እንዳሉት የስልጤ ህዝብ የሚፈልገውን ልማትና ዕድገት ከዳር ለማድረስ ቁልፍ መሳሪያ ትምህርት ነው።
አሁን ላይ በዞኑ እየተመዘገበ ያለውን ዕድገት ቀጣይነትና ዘላቂነት ዓለም አቀፍ ትርጉም ያለው እንዲሆን ለማስቻል ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ነው ያሉት ዴኤታው።
በዞኑ ለተመዘገበው ውጤት የጎላ አስተዋፅኦ ላበረከቱ መምህራንና ባለድርሻ አካላት እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን እነዚህን የሽልማት ቁሳቁስ ድጋፍ ረገድ የዞኑን የትምህርት እድገት አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ያለው የወራቤ ዩኒቨርሲተ ለዚህ ፕሮግራምም ከ100 በላይ ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችን ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።
Image