Skip to main content
የብሔራዊ ፈተና ውጤት የማትጊያ ፕሮግራም
=============================
በትምህርት ተደራሽነት ላይ የተመዘገበው ሰፊ ድል በትምህርት ጥራትም ሊደገም ይገባል ተባለ፡፡
በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የሚገኘውና በስልጤ ልማት ማህበር የሚደጎመው ሀይረንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በ2011 የትምህርት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚሄዱ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የአሸኛኘትና የማትጊያ ፕሮግራም አካሄዷል፡፡
በማትጊያ ፕሮግራሙ ላይ በ2010 ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲሁም የትምህርት ቤቱ መምህራንና ሌሎች ለውጤቱ መምጣት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በዚህም መሰረት በትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችና መምህራን የትምህርት ቁሳቁሶች እንዲሁም የገንዘብ ሽልማት በስልጤ ልማት ማህበር በኩል የተበረከተ ሲሆን በሌላ በኩልም በ2010 ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 98 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ላፕቶፕ ኮምፒውተር ፥ ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችና የገንዘብ ሽልማትን ጨምሮ አዲስ አበባ በሚገኘው ‹‹መላዬ›› የስልጤ ተወላጅ የንግድ ማህበረሰብ እድር አማካኝነት ተበርክቷል፡፡
‹‹መላዬ›› የስልጤ ነጋዴዎች እድር ከላፕቶፕና የቁሳቁስ እርዳታው በተጨማሪ ለ98ቱም ተማሪዎች የዩንቨርሲቲ ቆይታቸው የሚሆን የ500 ብር ክፍያ በየወሩ እንደሚከፍላቸው ቃል ገብቷል፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም በዞኑ ውስጥ በሚደረጉ የትምህርትና ሌሎች የልማት ስራዎች የሚችለውን ሁሉ እንደሚያግዝ መላዬ እድር በተወካዩ በኩል መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በማትጊያና የአሸኛኘት ፕሮግራሙ ላይ የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳዳር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ፣ የፌዴራሉ ህብረት ስራ ኤጀንሲ አቶ ኡስማን ሱሩር፣ የዞኑ የቀድሞ አስተዳዳሪዎች አቶ ጀማል ረዲና አቶ መዘረዲን ሁሴን፣ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ፣ የመላዬ እድር አባላት፣ የየምበሪማ ማህባር አባላት፣ ባለሀብቶች፣ ሌሎች ከፌዴራል እስከ ወረዳ የሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ዝግጅቱን በተመለከተ በትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ በአምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና በዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በተላለፉ መልዕክቶች ባለፉት ዓመታት በዞኑ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሰራው የጋራ ስራ የተገኘው ድል በትምህርት ጥራቱም ሊደገም ይገባል ተብሏል፡፡ ተሸላሚ የሀይረንዚ ተማሪዎችም ውጤታማነታቸውን ዘላቂ በማድረግ ሳይማር ያስተማራቸውን ህብረተሰብ ችግር ለመቅረፍ አልመው እንዲማሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡ በሀይረንዚ ደረጃ የተመዘገቡ ውጤቶች ወደ ሁሉም ት/ቤቶች እንዲሸጋገሩና ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲፈጠርም አሁን ያለው አመራር፣ ባለሀብቱ፣ መላው ህዝብና ሌሎች አጋሮች በቅንጅት እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡
Image