Skip to main content
በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የሀይረንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት የሽልማትና የምስጋና መርሃ ግብር ተከናወነ፡፡
ወራቤ፣ ህዳር 7/2017 (ስልጤ ዞን ኮሙኒኬሽን)
በ2016 ትምህርት ዘመን በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የሀይረንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ለውጤቱ መመዝገብ ልዩ አስተዋጽኦ ለነበራቸው ባለድርሻ አካላት የማበረታቻ ሽልማትና የምስጋና መርሃ ግብር በስልጤ ባህል አዳራሽ ተከናውኗል፡፡
የስልጤ ዞን አስተዳደር ከስልጤ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ባዘጋጁትና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽኝት ማድረግን ዓላማው ባደረገው በዚህ የሽልማትና የምስጋና መርሃ ግብር ላይ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 104 ተማሪዎችን ጨምሮ መምህራን ርዕሰ መምህራንና ሌሎች ከዞኑ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 5 ተማሪዎች ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በዚህም መሰረት የተሻለ ውጤት አምጥተው ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉ 104 የሀይረንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች እንደ ውጤታቸው ቅደም ተከተል በአራት ምድቦች ተከፍለው 20ሺህ ብር፣ 15 ሺህ ብር፣ 10 ሺህ ብር እና 3 ሺህ ብር ሲሸለሙ ሌሎች ከዞኑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ 5 ተማሪዎች እንደ ውጤታቸው ቅደም ተከተል የ20 ሺህ እና 10 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
በሌላም በኩል ለተማሪዎች የተሻለ ውጤት መመዝገብ የላቀ ሚና የነበራቸው የ12ኛ ክፍል መምህራን በሶስት ምድቦች ተከፍለው የ15 ሺህ ብር፣ የ12 ሺህ ብር እና የ10 ሺህ ብር ሽልማት ሲበረከት ለአጠቃላይ የሀይረንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የሰርተፊኬትና ሜዳሊያ ስጦታ ተበርክቷል፡፡
ሀይንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በተሻለ ብቃት በመምራት ለውጤቱ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ለነበራቸው የትምህርት ቤቱ ዋና ርዕሰ መምህር የ20 ሺህ እንዲሁም ለምክትል ርዕሳነ መምህራን የ17 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቷል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ብልካን ጨምሮ የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ ነዒማ ሙኒር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ጸረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጀማል ረዲ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ደ/ር መሐመድ ሽኩር፣ የስልማ ቦርድ አባላት፣ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
Image